Article

Maranatha

January 21, 2026

የመስቀሉ ኃይል

ከዶክተር/ፓስተር ሐንፍሬ አሊጋዝ

(የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና መሪ)

1ኛ ቆሮ፡ 1፡18

18 የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። ተገረፈ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ፣ ተነሳ፣ የሚለው የመስቀሉ ቃል በጣም ታላቅ ነው ለእኛ ለምንድን። መስቀሉ እግዚአብሔር ለሰዎች ያለውን አላማ የገለጠበት ነው፣ መስቀሉ የክርስትና ዕምነት መሰረት ነው። ስለዚህም መሰረታችን መስቀል ነው። መስቀሉ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ የጥያቄ መልስ አለው። መስቀሉ የደህነታችን አቅድ የተገለጠበት ነው። መስቀሉ ኃይል ነው፣ በመስቀሉ ላይም የተሠራው ሥራ በጣም ትልቅ ነው፣ ለማያምኑት ግን ሞኝነት ነው፣ ለሚያምኑ ግን ኃይል ነው፣ ያውም የእግዚአብሔር ኃይል። ስለዚህ ስለ መስቀሉ ስንመለከት የምናያቸው በርካታ ነገሮች አሉ፤


1. የእግዚአብሔር ፍቅር ለዓለም ሁሉ ሕዝብ የተገለጠበት ነው፤ ዮሐ 3፡16

16 በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም ሁሉ የተወደደበት ፍቅር ነው፣ ምንም ልዩነት ሳይደረግ ትልቁ ከትንሹ፣ ጥሩው ከመጥፎው ፣ ደሃው ከሀብታሙ ሳይለይ የተወደደበት ፍቅር ነው። የተወደድነውም ገና ኃጥያተኞች ሳለን ነው። ሮሜ 5፡8 ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። እዚህ ላይ የሚገርመው ነገር፤ እኛ በእግዚአብሔር ፍቅር የተወደድንበትን በማስታወስ ነው መመክት የሚገባን እንጂ እኛ እግዚአብሔርን በመውደዳችን ላይ ሊሆን አይገባም። የእኛ እግዚአብሔርን መውደድ ብቻ በቂነት የለውም፣ አስተማማኝነትም የለውም። ጴጥሮስ ጌታን በጣም ይወድ ነበር፣ ለጌታም ለራሱ እንደሚወደው ይነገረው ነበር፣ እስከሞት ድረስ አልክድህም ብሎ ከተናገረው በኋል፣ ፈታኝ ወቅት ሲመጣ ግን ካደው። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ስንመለከት ሃዋርያው ዮሃንስ “ጌታ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር” የተባለት ሰው ነበር። ሃዋርያው ዮሃንስ ተደግፎ የነበረው ጌታ በሚወደው ላይ ነበር እንጂ እሱ ጌታን በሚወደው ላይ ፍቅር የተመረኮዘ ሰው አልነበረም። ስለዚህም እስከመጨረሻው ወቅት፣ ጌታ እስከሚሰቀል መጨረሻው ድረስ አብሮት የነበረና ሲሰቀል የተመለከተ ደቀ መዝሙር እሱ ብቻ ነበር። ምክንያቱም የዮሃንስ ፍቅር እኔ እወደዋለው ማለት ብቻ ሳይሆን ጌታ በእሱ ላይ ያስቀመጠውን ፍቅርና እንዴት ጌታ እሱን እንደሚወደው ያውቅ ስለነበር ነው። የእኛ ፍቅር ምንም የሚያስመካን ሊሆን አይገባም። የሚያስመካን ጌታ ለእኛ ያለው ፍቅር ሊሆን ይገባል። እኔ እወደዋለው እያሉ አይደል ብዙ ሰዎች ወደኃላ የተመለሱት፣ ጥለውት የሄዱት። ስለዚህ ጌታ እኔን ይወደኛል፣ አይተወኝም ብለን ሁል ጊዜ ልናስብ ይገባናል። የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው ተብሎ ተጽፏልና።


2.  መስቀሉ ጌታ ለእኛ ያለውን ፍቅር የተገለጠበት ቦታ፤ ዮሐ 15፡13

13 ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። ጌታ በመስቀል ላይ ፍቅርን ነው ያስተማረን፤ እኛም ሌሎችን እንድንወድ። የፍቅር መነሻው እግዚአብሔር ነው፣ ፍቅር ከሌላ ቦታ አይመጣም፣ ምንጩ እግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ። ልንማርም የሚገባን ከምንጩ ነው፤ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ። እሱ ምሳሌ ሆኖ ስላስተማረን ሌሎችን ልንወድ እንችላለን። መስቀሉ የሚያስተምረን እግዚአብሔር በክርስቶስ ያደረገውን እኛ ደግሞ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የምናደርግበትን ያስተማረበት ቦታ ነው። እርስ በርሳቹ ትዋደዱ ዘንድ፣ እኔ እንደ ወደድኳቹ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳቹ ትዋደዱ ዘንድ አዲስን ትእዛዝ ሰጠኋችሁ። ትእዛዙ አዲስ የሆነበት ምክንያት፣ ከጥንቱ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮም ባልንጀራህን እንደ ራስ ውደድ የሚል ትእዛዝ አለ፣ ኢየሱስ ግን ያስተማረን እኔ እንደ ወደድኳቹ የሚለው ቃል ነው፤ ምክንያቱም የእሱ ፍቅር በመስቀል ላይ ታይቷልና። አዲስ የሚያደርገው ትእዛዙን እሱ እኛን እንደወደደን እኛም ደግሞ ሌሎችን እንድንወድ ያስትምረናል። 


3. በመስቀሉ ከኃጢአት ባርነት ነፃ ወጣን፤ ሮሜ 6፡20

20 የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና። ኃጢአት አይገዛንም፤ አልጠላም፣ አልዋሽም፣ ተንኮል አላደርግም ብለን ከተናገርን ብኋላ ስንት ጊዜ ነው ደግመን ስናደርግ የምንገኘው፤ የኃጢአት ባሪያዎች በመሆናችን ነበር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ኃይል፣ በጌታችን ኢየሱስ ፀጋ ኃጢአትን ሁሉ የሚያስክድ ፀጋ ስለተሰጠን በፀጋው ከኃጢአት ባርነት ወተናል። ኃጢአት ክፉ ነው፣ የኃጢአት ደሞዝ ደግሞ ሞት ነው። የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ ግን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት ነው። ኃጢአት ሰውን ፈሪ ያደርጋል፣ ኃጢአት ማንም ሳያባርረው ይሸሻል። ምሳሌ 28፡1 ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል። ጌታ በመስቀል ላይ የኃጢአትን ሥራ አፈረሰው እኛ ደግሞ በእሱ ሆነን ነፃ ሆንን። 


4. በመስቀሉ ሥራ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀን ሮሜ 5፡19

19 በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር የተጣላን ነበርን፣ ጌታ ግን እዳችንን ከፍሎ፣ በደሙ አጥቦ፣ ኃጢአታችንን አስወግዶ ለአባቱ ካህናት እንሆን ዘንድ አበቃን፣ በፊቱ አቀረበን፣ አስታረቀን። አንዳንዴ ሰዎች እንዴት በማመን ብቻ ሰው ይጸድቃል ይላሉ፣ በአንዱ ኃጢአት በመስራት ብቻ ነው ሁላችን የወደቅነው፤ ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ ጽድቅን በማድረግ በአንዱ ብቻ ደግሞ ወደ ጽድቅ እንመጣለን። እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ያዘጋጀው የድህነት መንገድ በጣም የሚያስገርም ነው።

ሮሜ፡5፡9

9 ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። ከእግዚአብሔር ጋር የተጣላን ሰዎች ነበርን፣ በልጁ ግን አስታረቀን። በእርሱ ሥራ ሁላችን ወደ አብ መግባት ሆነልን። የእኛ ሥራ ምንም የሌለበት፣ ወደ አብ የቀረብነው በእሱ ሥራ፣ መንግስተ ሰመዓት የገባነው በእሱ ሥራ፣ የእግዚአብሔር ልጆች የሆነው በእሱ ሥራ፣ ሁሉ የሆነው ኢየሱስ በሠራው ሥራ ነው። ሁላችንን ሰብስቦ የአንድ አገር ዜጋ አደረገን፣ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች አደረገን።

share this

Related Articles

Related Articles

ALL ARTICLES